ደ.መ ኢየሱስ

ቅዱስ ጋብቻ

ጋብቻ ምንድን ነው?

ጋብቻ በሁለት ተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚደረግ የአእምሮና የሥጋ ውህደት ነው። ጋብቻ የሚመሰረተው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ነው።

ጋብቻን ማን መሰረተው?

ጋብቻን የመሰረተው ልዑል እግዚአብሔር ነው የተመሰረተውም በመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአዳምና በሔዋን ነው። የመጀመሪያው ጋብቻ የተመሰረተው በኤደን ገነት ነው።

እግዚአብሔር እንደ አባት እንደ እናት ሆኖ መላእክት አጅበዋቸው ጋብቻን ለአዳምና ሔዋን ባርኮ ሰጥቷቸዋል። ጋብቻን ሰው በራሱ ፈቃድና ጥበብ የመሰረተው ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብና ፈቃድ የተመሰረተ ነው።

"እግዚአብሔር አምላክም አለ፡— ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።" ዘፍ 2: 18

ለሰው በብቼኝነት መኖር መልካም አለመሆኑን የተናገረለትና ጋብቻን የወሰነለት እግዚአብሔር ነው ለዚህም ፈጣሪው ስለሆነ ባህርዩን ያውቀዋል። ረዳቱንም የፈጠረለት ከሌላ አካል ሳይሆን ከራሱ ጎን ነው።

"እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፡— ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። " ዘፍ 2:21

በመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን የተጀመረው ጋብቻ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሲፈፀም ይኖራል። ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ የሰጠ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳንም የጋብቻን ቅዱስነት እና ክቡርነት እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ለብሶ በምድር ላይ ሲመላለስ አረጋግጧል።

ፈሪሳውያን ስለመፋታት በጠየቁት ጊዜ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለኝ ብሎ ያለዝሙት ምክንያት መፋታት እንደማይቻልና ጋብቻ ቅዱስ መሆኑን አጠንክሮ ነግሯቸዋል።

"ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው። " ማቴ 19 : 3

እንዲሁም በቃና ሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ የመጀመሪያውን ተአምር በማድረግ የጋብቻን ቅዱስነት አረጋግጧል። ዮሐ 2:1 -11

ሐዋርያትም ይህንን አጠንክረው ጽፈዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል።

"መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።" ዕብ 13:4

የጋብቻን አስደናቂ ምሥጢርነት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እያለ ይገልፀዋል

"ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።" ኤፌ 5:31

ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የክርስቶስን ቃልና የሐዋርያትን ትምህርት መሠረት አድርጋ ጋብቻ የተቀደሰ መሆኑን አውቃ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዱ ምሥጢረ ተክሊል እንዲሆን አድርጋለች። ይህንንም እያስተማረች ልጆቿን በስርዓተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን ትሞሽራለች ታከብራለች።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጋብቻን አላማ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች መድባ ታስተምራለች።

የጋብቻ አላማ

1. እርስ በእርስ ለመረዳዳት

"እግዚአብሔር አምላክም አለ፡— ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍ 2:18

አዳም የምትመቸው ረዳት እንደምታስፈልገው ያወቀለት እና የወሰነለት ፈጣሪው እግዚአብሔር ነው ባህርይውን ያውቃልና ስለዚህ ከጋብቻ አላማ አንዱ መረዳዳት መሆኑን በዚህ መረዳት እንችላለን። ጠቢቡ ሰሎሞንም እንዲህ በማለት ይገልፀዋል

"ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፤ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? " መጽሐፈ መክብብ 4:9

መረዳዳት ሁለቱም ያላቸውን እኩል አቅም በአንድነት አስተባብረው ሕይወትን ተጋግዘው የሚያልፉበት ጉዞ ነው። ይህም በአንድ ቀንበር እንደተጠመዱ በሬዎች ማለት ነው።

አንደኛው መሳቡን ቢያቆም እርሻው በትክክል ሊታረስ እንደማይችል ሁሉ በትዳርም ውስጥ ሁለቱም በተጠመዱበት የትዳር ቀንበር ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ ትዳር የሰመረ ይሆናል።

እርስ በእርስ ለመረዳዳት ሲባል ይህ በጋብቻ ውስጥ ያለው መረዳዳት ከሌሎች መረዳዳቶች የተለየና የጠለቀ ነው ። በጥልቅ ስሜት መተዋወቅ ማለት ነው። ለባል የሚስትን ረዳትነት የሚተካ ነገር የለም ለሚስትም የባልን ረዳትነት የሚተካ ነገር የለም። በሁለቱ መካከል ያለው መረዳዳት ጥልቅ ነው።

2. ዘርን ለመተካት

ሁለተኛው የትዳር አላማ በምድር ላይ ዘር እንዲተካ ነው። ጋብቻ ባይኖር ኖሮ ትውልድ ባልኖረ ነበር ። ቅዱሳን ጳጳሳት ቀሳውስት ዲያቆናት ምዕመናን ነገሥታት በዚህ ምድር የሚንቀሳቀስ ትውልድ ሁሉ የሚገኙት ከጋብቻ ነው። ይህም ከእግዚአብሔር በበረከት የተሰጠ ፀጋ ነው እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በሗላ ለሰው ልጅ የሰጠው በረከት ይህ ነው።

"እግዚአብሔርም አለ፡— ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፡— ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።" ዘፍ 1:26

በሰው ልጅ ኃጢአት ምክንያት ምድር በማየ አይኅ ተጥለቅልቃ ትውልድ ሁሉ ተደምስሶ ኖኅና ቤተ ሰቡ በቀሩ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ በዚህ በረከት እንደገና ባርኳቸዋል።

እንዲህ ሲል

"እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው፡— ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት። አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል። ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ። ዘፍ 9: 1

በጋብቻ የሚገኙ ፍሬዎችም የእግዚአብሔር በረከትና ስጦታ መሆናቸውን ቅዱስ ዳዊት እንዲህ በማለት ይገልፀዋል።

"እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው ። የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።" መዝ 126: 3

3. ከፍትወት ፆር ለመዳን

በባልና ሚስት መካከል ያለውን የመፈላለግ ስሜት የፈጠረላቸው እግዚአብሔር ነው። በአዳም ውስጥ እግዚአብሔር የፍትወትን ስሜት ባያኖር ኖሮ ሔዋንን ሲያያት አዳም ይህች አጥንት ከአጥንቴ ሥጋም ከሥጋዬ ብሎ አይቀርባትም አያቅፋትም ነበር። አፒታት (የምግብ ፍላጎት) ባይኖር ኖሮብ ምግብ መብላት ባልኖረም ነበር።

ስለዚህ ፍትወት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ፀጋ በመሆኑ ይህንን ፍትወት በተገቢው መንገድ በሚገባ የተፈቀደ ጋብቻ መፈፀም ይገባል እንጂ ያለ አግባብ በዝሙት መንገድ መፈፀም በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው።

በተቀደሰ ጋብቻ የሚደረግ ግንኙነት ቅዱስና ንፁህ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል።

"መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።" ዕብ 13:4

በሌላም ስፍራ እንዲህ ይላል

" ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።" 1ኛ ቆሮ 7:2

ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አላማዎች በጋብቻ ውስጥ ወሳኝ አላማወች ናቸው።

ክርስቲያናዊ ጋብቻ

ክርስቲያናዊ ጋብቻ ከሌሎች ጋብቻዎች ይለያል ። ክርስቲያን እንደቃሉ የሚኖር እንጂ በዘፈቀደ የሚኖር ባለመሆኑ ጋብቻንም የሚፈፅመው እንደ እግዚአብሔር ቃል እና ትእዛዝ ነው። ስለዚህ ክርስቲያናዊ ጋብቻ የሚከተሉት መስፈርቶችን የሚያሟላ መሆን አለበት

1. በሃይማኖት ከማይመሳሰል ጋር አይፈፀምም

ክርስቲያናዊ ጋብቻን በሃይማኖት ከማይመስል ( ከማትመስል ) ጋር መፈፀም ፈፅሞ የተከለከለ ነው። ክርስቲያናዊ ጋብቻ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው ። ስለዚህ በሃይማኖት ከማይመስል ጋር መፈፀም ምሥጢሩን ያፈርሰዋል።

" ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። "

" ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላልሁሉንም የሚገዛ ጌታ።" 2ኛ ቆሮ 6:14

ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ጋብቻን ሊፈፅም ሲያስብ የመጀመሪያው መመዘኛ በሃይማኖት የሚመሳሰል መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ይህ ካልተሟላ ማቆም አለበት ነገር ግን በሃይማኖት የማይመሳሰሉ ሆነው አስተምሮ አስጠምቆ ግን ማግባት ይቻላል።

በክርስቲያናዊ ጋብቻ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት በላይ አንዲት ሴትም ከአንድ ወንድ በላይ ሊያገቡ አይችሉም እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋንን ነው የፈጠረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈሪሳውያን ሚስትን ስለመፍታት በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ነው ያላቸው

2. አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ብቻ

በክርስቲያናዊ ጋብቻ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት በላይ አንዲት ሴትም ከአንድ ወንድ በላይ ሊያገቡ አይችሉም እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋንን ነው የፈጠረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈሪሳውያን ሚስትን ስለመፍታት በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ነው ያላቸው

" ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም" ማቴ 19:3

3. በሥጋዊ ዝምድና እስከ ሰባት ትውልድ መራቅ ያስፈልጋል

ከሰባት ትውልድ ባንሰ ዝምድና ውስጥ ክርስቲያናዊ ጋብቻ አይፈፀምም።

5. እስከ ጋብቻ ድረስ ድንግልናን ጠብቆ መቆየት

ድንግልናን ጠብቆ ማግባት በትዳር ውስጥ ብዙ በረከት ያሰጣል

  • መልካም ዘር ያሰጣል
  • ትዳር ይባረካል
  • ሰማያዊ በረከት ያሰጣል

ክርስቲያናዊ ጋብቻ እንዴት ይፈፀማል?

ክርስቲያናዊ ጋብቻ የሚፈፀመው በስርዓተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን ነው። ክርስቲያናዊ ጋብቻ ከዚህ ውጪ አይፈፀምም። ፍት ነገ አንቀፅ 24 ምዕ 25:ክፍል 2

ባል ለሚስቱ ምን ማድረግ ይገባዋል?

ባል ሚስቱን እንደገዛ ሥጋው አድርጎ ሊወዳትና ሊንከባከባት ይገባል።

" ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። " ኤፌ 5:25

" ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ። " ኤፌ 5:33

" እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው። " 1ኛ ጴጥ 3:7

" ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ። ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ። ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፡— እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው።" 1ኛ ቆሮ 7:3

ሚስት ለባልዋ ምን ማድረግ ይገባታል?

ባልዋ እንደወደዳት እርሷም እርሱን ልትወደውና ልትታዘዘው ይገባታል።

" ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።" ምሳ 12:4

" ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል። የባልዋ ልብ ይታመንባታል። ምርኮም አይጐድልበትም። ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። የበግ ጠጕርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች። " ምሳ 31:10

"እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፡— ጌታ፡ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ።" 1ኛ ጴጥ 3:1

"ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው። " ቆላ 3:18