ደ.መ ኢየሱስ

ቅዳሴ

የእሁድ Dec 26

(**ጥቅሶቹን ነክተው አምስቱን ንባባት ያግኙ**)

ሮሜ 13:11-ፍጻሜ

11 ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና።

12 ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።

13 በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤

14 ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።

1ኛ ዮሐ 1:1-ፍጻሜ

1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤

2 ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤

3 እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።

4 ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።

5 ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።

6 ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤

7 ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።

8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።

9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።

10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

የሐ ሥራ 26:12-ፍጻሜ

12 ስለዚህም ነገ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥

13 ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤

14 ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ።

15 እኔም። ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።

16 ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና።

17 - 18 የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።

19 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም።

20 ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ።

21 ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ።

22 - 23 ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።

24 እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ። ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል አለው።

25 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ። ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም።

26 በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና።

27 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።

28 አግሪጳም ጳውሎስን። በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ አለው።

29 ጳውሎስም። በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ አለው።

30 ንጉሡም አገረ ገዡም በርኒቄም ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፥

31 ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ ብለው ተነጋገሩ።

32 አግሪጳም ፈስጦስን። ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር አለው።

ምስባክ: መዝ 43:3

ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሐኒ ውይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ

ትርጉም፦

"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።"

የዕለቱ ወንጌል: ዮሐ 1:1-ፍጻሜ

1 በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።

2 ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።

3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።

4 በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።

5 ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።

6 ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤

7 ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።

8 ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።

9 ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።

10 በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።

11 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።

12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤

13 እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

14 ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።

15 ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።

16 እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤

17 ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።

18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።

19 አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።

20 መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።

21 እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ።

22 እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት።

23 እርሱም። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።

24 - 25 የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።

26 ዮሐንስ መልሶ። እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤

27 እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።

28 ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።

29 በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።

30 አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።

31 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።

32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።

33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።

34 እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።

35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥

36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።

37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

38 ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ። ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው።

39 እነርሱም። ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው።

40 መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ።

41 ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ።

42 እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።

43 ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው።

44 በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው።

45 ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።

46 ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።

47 ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው።

48 ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።

49 ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።

50 ናትናኤልም መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።

51 ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።

52 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።

ከላይ የተጠቀሱትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንብበው ሥርዓተ ቅዳሴውን የተመዘገባችሁ በቤተክርስቲያን ወይም dmeyesus youtube channel ይከታተሉ ከበረከቱም ይካፈሉ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።


ቅዳሴ ምን ማለት ነው?

ቅዳሴ - ማለት ቀደሰ ካለዉ የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን - ትርጉሙም - አመሰገነ ፣ አከበረ ፣ ለየ … ማለት ነው። በዚህ አውድ ቅዳሴ ማለት ምስጋና ማለት ነው።

ቅዳሴ መቼ ተጀመረ?

አባቶቻችን ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ እንዲሉ ስለ አንድ ነገር ሲነሳ መነሻውን ማወቅ ይጠቅማልና ቅዳሴ ከየት መጣ? የሚለውን ጥያቄ መልሶ ማለፍ ተገቢ ነው። ቅዳሴ የተጀመረው በመላእክት ነው። መላእክት መፈጠራቸው ለምስጋና እንደመሆኑ መጠን ፤ መላእክት ሲፈጠሩ ምስጋና/ቅዳሴ/ ተሰጥቷቸዋል። በመጽሐፈ ኢዮብ 38 ÷ 6 ላይ የተጻፈውን ስንመለከት እንዲህ ይላል።

“አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ የእግዚያብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ መሠረቶቿ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማነው?”

በእርግጥ መላእክት ሳይፈጠሩ እግዚአብሔር ምስጋናው አልተቋረጠበትም። ማን ያመሰግነው ነበር ቢሉ ባሕርዩ ባሕርዩን ያመሰግነው ነበር መላእክት የተፈጠሩት በባሕርዩ ተሰውሮ የነበረውን ምስጋና እንዲገልጡ ነው። መላእክት በማመስገናቸው እነሱ ይከብራሉ እንጂ እግዚአብሔርን ክብር አይጨምሩለትም። እርሱ በባሕርዩ ክቡር ነውና። ዲያብሎስ አላመሰግንም በማለቱ እርሱ ክብር ቀረበት እንጂ እግዚያብሔርን አላጎደለበትም። እርሱን የሚያመሰግኑ እልፍ አእላፍ መላእክት አሉትና። የመላእክት ስራቸው ምስጋና-ቅዳሴ ነው። ይህንንም ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ያየውን እንዲህ በማለት ይገልጻል።

“ንጉስ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት። የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር እያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፤ በሁለትም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚያብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት።” - ኢሳ 6 ÷ 1

ኢሳይያስ እነዚህ ነገሮች ሲከናወኑ ያየዉ በሰማይ ባለችው መቅደስ ነው።

በመላእክት ቅዳሴ ውስጥ ምን አለ?

  • መቅደስ አለ
  • መስቀል አለ
  • ተሰጥኦ አለ
  • እጣን አለ

የመልአኩ ክንፍ ወደ ላይና ወደታች ፡ ወደቀኝና ወደግራ መሆኑ መስቀል ነው። አንዱ ለአንዱ ሲል ተሰጥኦ መቀባበልን ያመለክታል። ቤቱንም ጢስ ሞላበት - ሲል ዕጣኑን ያመለክታል። “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።” - ራዕ 8 ÷ 4

እነዚህ በሰማይ ባለችው መቅደስ የሚከናወኑ ናቸው። እነዚህን ነገሮች አሟልታ የተገኘች ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት። በቅዳሴያችን ውስጥ እነዚህ ሁሉም አሉ፡

  • መቅደስ አለ
  • መስቀል አለ
  • ተሰጥኦ አለ
  • እጣን አለ

ዝቅ ይልና ኢሳይያስ እንዲህ ይላል ፡-

“ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢኣትህም ተሰረየልህ አለኝ።” - ኢሳ 6 ÷ 6

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ደግሞ ሦስት ነገሮችን እናገኛለን ፡-

  • መሰዊያው
  • ፍሕሙ
  • ጉጠቱ

መልአኩ ከመሰዊያው በጉጠት የወሰደው ፍሕም ነበር ይላል። መልአኩ ፍሕሙን የያዘው በጉጠት ነው። ለምን በጉጠት ያዘው? እንዳያቃጥለው እንዳንል መላእክት ተፈጥሮአቸው ከእሳትና ከነፋስ ነው።

“መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል” - መዝ 104 ÷ 4 ​

“ስለ መላእክትም መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ” - ዕብ 1 ÷ 7​

ታዲያ መልአኩ ራሱ እሳት ከሆነ ለምንድን ነው ፍሕሙን በጉጠት የያዘው ስንል ፡-

  • ፍሕሙ - የክርስቶስ ስጋና ደም ምሳሌ ነው።
  • ጉጠቱ - የዕርፈ መስቀል ምሳሌ ነው።

መልአኩ ፍሕሙን አለመንካቱ መላእክት የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመፈተት አልተሰጣቸውምና ይህ ሥልጣን የተሰጠው ለካህናትvነው። ለዚህ ነው "ዘኢተገብረ ለመላእክት ተገብረ ለካህናት" ‘ለመላእክት ያልተደረገ ለካሕናት ተደረገ’ የተባለው። ካህናት በሥልጣናቸው መልአከ ሞትን ገዝተው እንዳቆሙ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ታሪክ ታይቷል። ዮሐንስ አፈወርቅ መልአከሞትን ገዝቶ አቁማል።

ቅዱስ ጳውሎስም “የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳን እንድንፈርድ አታውቁምን?” – 1ኛ ቆሮ 6 ÷ 3 ይህ ምሥጢር ዛሬ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ይከናወናል።
  • መሰዊያው አለ- መንበሩ ጽላቱ ነው።
  • ጉጠቱ አለ - እርፈ መስቀሉ ነው

ሥጋውን ካህኑ በእጁ ሲፈትትና ሲያቀብል ፣ ደሙን ደግሞ ዲያቆኑ በእርፈ መስቀሉ ያቀብላል። ኢሳይያስ በፍሕሙ ከለምጹ እንደተፈወሰ ዛሬም ሥጋውና ደሙ ከነፍስና ከሥጋ ደዌ ምዕመናንን ይፈውሳልና። ኢሳይያስ በፍሕሙ ተፈወሰ ስንል በቁሙ ፍሕም ቢሆን ኖሮ ፍሕም ያቃጥላል በቁስል ላይ ቁስል ይጨምራል እንጂ አይፈውስም። ምሥጢሩ ግን አማናዊው ፈዋሹ የክርስቶስ ሥጋና ደም አስቀድሞ በምሳሌ መገለፁ ነው። ልክ እስራኤል በበጉ ደም ከሞተ-በኩር እንደዳኑት። በቁሙ ቢሆን ኖሮ የበግ ደም ከሞት አያድንም። በጉ የጌታ ምሳሌ ደሙ የክርስቶስ ደም ምሳሌ ነው። "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢኣተ ዓለም" የዓለምን ኃጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" አለ ቅዱስ ዮሐንስ ዮሐ 1 ÷ 40

በብሉይ ኪዳን ኢሳይያስ ያየው ቅዳሴም በሐዲስ ኪዳን አልተቋረጠም። የሐዲስ ኪዳን ቅዳሴ የተጀመረው በቤተልሔም ነው። ጌታ በተወለደ ጊዜ ሰውና መላእክት በአንድ ላይ ሲያመሰግኑ የሐዲስ ኪዳን ቅዳሴ ተጀምሯል። የሥርዓተ ቁርባን ምሥጢር የተጀመረው ደግሞ በምሴተ ሐሙስ ነው። “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ማቴ 26 ÷ 26 ከጌታ የተቀበሉትን ሥርዓትም ሐዋርያት ይፈጽሙት ነበር። “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ በሐዋርያትም ትምሕርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። የሐ 2 ÷ 41 እንጀራውንም በመቁረስ ሲል ሥጋውን ደሙን እየፈተቱ ሲል ነው ፤ ስለ ተራ እንጀራ መቁረስ ሉቃስ ገዶት አይደለም። ጌታ እንጀራውን ባረከ ቆርሶም ሰጣቸው እንዳለው ነው። ይህ አሁን እንጀራ ስለተባለ ተራ እንጀራ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ 11 ÷ 24 - 31 ላይ የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር በሚገባ ገልፆታል፡-

“ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና። ስለዚህ በእናንተ ዘንድየደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤” 1ኛ ቆሮ 11 ÷ 24 - 31​​

ስለዚህ የቅዳሴና የቁርባንን ሥርዓት የእኛ ቤተ-ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በድንገት ያመጣችው ሳይሆን:-

  • በመላእክት በሰማይ ባለችው መቅደስ የሚከናወን
  • በሐዲስ ኪዳንም ቀጥሎ በቤተ ልሔም በመላእክትና በሰዎች ኅብረት የተከናወነ
  • የቁርባኑን ሥርዓት ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረተው በሐዋርያትም ዘመን ይፈፀም የነበረ ሥርዓት ስለሆነ ቤተ-ክርስቲያናችን ይህንን ሥርዓት ተቀብላ ትፈጽማለች።

ይህ የቅዳሴ ሥርዓት በሐዲስ ኪዳን አለመቋረጡን የበለጠ ግልፅ የሚያደርግልን ደግሞ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ያየውን ከብዙ ዓመታት በኋላ ወልደ ነጎድጓድ ዮሐንስ ማየቱ ነው። (ራዕ 4 ÷ 1) ኢሳይያስ ያየውን ነው ዮሐንስ ያየው ምሥጋናቸውም አልተለወጠም -ምሥጋናቸው “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ነበር። በዚህ ረጅም ዘመን የመላእክት ምሥጋና አልተለወጠም የእኛም ቅዳሴ የማይለወጠው የመላእክት ቅዳሴ ስለሆነ ነው። ይህንን ያልተረዱ ሰዎች ፡ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ነው፣ረዘመ፣ለምን ከዘመን ጋር አብሮ አይለወጥም? የሚሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ እንሰማለን። የማይለወጥበት ምክንያት ግን የመላእክት ምስጋና ስለሆነ ነው። “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ከማለት የበለጠ ምስጋና የለም።