ደ.መ ኢየሱስ

ጥምቀት/ክርስትና

ምሥጢረ ጥምቀት

ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዱ ሲሆን ከማይደገሙ ምሥጢራት ውስጥ ነው። የሐዲስ ኪዳንን ጥምቀት የመሰረተው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

በሦስት መንገድ መስርቶታል

1. በተግባር

በ30 ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ጥምቀትን በተግባር መስርቶልናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ፈልጎ ሳይሆን ለእኛ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን ነው።

"ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደየምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።" ሉቃ 3:21

2. በትምህርት

የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሄደ ጊዜ የምሥጢረ ጥምቀትን ነገር ገልጾ አስተምሮታል።

እንዲህ ሲል-

"ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። " ዮሐ 3:5

ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን አመስጥሮ ተናግሮታል።

"ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። " 1ኛ ዮሐ 5:5

3. በትእዛዝ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን ራሱ ተጠምቆ ከመሰረተልን በሗላ በትእህርትም ካስተማረ በሗላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል አዟቸዋል-

"እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸውእነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።" ማቴ 28:20

"እንዲህም አላቸው። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።" ማር 16: 15

ቤተ ክርስቲያንም የጌታችንን ትእዛዝ የሐዋርያትን ትምህርት መሠረት አድርጋ ምእመናንን ወንድ በተወለደ በአርባ ቀን ሴት በተወለደች በሰማንያ ቀን እያጠመቀች የሥላሴን ልጅነት ታሰጣለት። ጥምቀት ወደ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር ናት። ያልተጠመቀ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገባና ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሊቀበል አይችልም። በጥምቀት ዳግመኛ ከማይጠፋ ዘር እንወለዳለን።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን እንዲህ በማለት ይገልፅልናል-

"ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።" 1ኛ ጴጥ 1:23