የደብረ መድኃኒት ኢየሱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውድብሪጅ ቨርጅንያ የሚጊኝ ሲሆን በአካባቢው በሚገኙ በጎ ምዕመናን ተነሳሽነት አሳቡ ከተጀመረ በኋላ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በማኅበርና በጸሎት እንዲሁም ወንጌልን በመማር ሲደራጅ ቆይቶ በ2610 Omisol Rd Woodbridge, VA 22192 አድራሻ በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ግንቦት 15/2002 (May 23, 2010) በዕለተ ጰራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ ለሐዋሪያት በወረደበት ቀን) ቅዳሴ ቤቱ ሊጀመር ችሏል። አገልግሎቱም ተጠናክሮ በመቀጠሉ የደብረ መድኃኒት ኢየሱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኮመን ዌልዝ ኦፍ ቨርጂንያ ስቴት ኮርፖሬሽን ኮሚሽን በሚባለው የመንግስት አካል በህዳር 12, 2004 ዓ.ም (Nov 22, 2011 ) በ501(c)(3) እውቅና አግኝቶ በህጋዊነት ተመዝገቡዋል።
ቤተ ክርስቲያኖችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ በመሄድ በአካባቢው ለሚገኙ ምዕመናንና ምዕመናት ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ275 በላይ የሚሆኑ ቤተሰብ አባላት ያሉት ቤተ ክርስቲያን ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ለተተኪው ትውልድ ትኩረት በመስጠት ህፃናት ልጆች ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያውቁ በዕለተ እሁድና በቀዳሚት ዕለት ትምህርት ቤት በመከራየት የሃይማኖት፣ የሰነ ምግባርና የቋንቋ ትምህርትን በማስተማር ትውልዱን በማነጽ ላይ ይገኛል። ከልጆቻችንም መካከል የዲቁና ትምህርትን በማስተማር ሦስት ዲያቆናትን ለማዕረገ ዲቁና አብቅቷል። ለወደፊቱም ይህንን አገልግሎትና ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።
በአሁኑ ሰዓት መደበኛ አገልግሎቱ የሚካሄደው በ5070 Dale Blvd Woodbridge VA 22193 ላይ በሚገኘው የኪራይ ቤት ሲሆን የራሳችንን ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ለማሰራት በታላቅ ርብርብ ላይ እንገኛለን።