ወንጌል የሚለው ቃል “ዩአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው በግእዙ ቋንቋ ብሥራት ይባላል። የግሪኩም ይሁን የግእዙ ትርጉም የምሥራች ማለት ነው።
ወንጌል በሚል ቃል የተጠራው የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱና ትምህርቱ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት የሠራው የአድኅኖት ሥራ ሁሉ ወንጌል ተብሏል። ወንጌል ከላይ እንዳየነው የምሥራች ሲሆን የልዑል አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ መወለዱን ስለሚያበሥር ነው። “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ሉቃ 2፡10
በዚህም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ቀደመ የልጅነት ክብሩ እንደተመለሰ ሲያስረዳ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች በማለት መልአኩ ለኖሎት አበሰራቸው ከዚህ የበለጠ የምሥራች የሚባል ምን አለ? የተወለደው የሁሉ መድኃኒት ነውና ሰውን ሁሉ አዳነ ይህ ለእኛ ከደስታ ሁሉ በላይ ደስታ ነው በምንም ዋጋ የማይተመን እግዚአብሔር ለእኛ የተሰጠበት የምስራች ቃል ነው። እንግዲህ ስብከተ ወንጌል ሲባል የወንጌል ትምህርት ሲሆን ይህም የምስራችን ቃል ላለተበሠሩ ማብሠር፣ ላልተሰበኩ መስበክ፣ ላልሰሙ ማሰማት ፣ማስተማር ፣ማስረዳት ፣ማሳማን ፣በቃለ ወንጌል አምነው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ከተሰጣት የአገልግሎት ሥራ ሁሉ ቀዳሚም ደኃሪም የምስራቹን ቃል መስበክ ነው። ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በማስተዋል እንመልከት።
“እንዲህም አላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ማር 16፡15
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላዓለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው” ማር 16፡8
“የወንጌል ሰበኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን ፈጽሞ” 2ጢሞ4፡5 “በጊዜውም አለጊዜውም ወንጌልን ስበክ”