ደ.መ ኢየሱስ

የሰንበት ት/ቤት

ሰንበት ት/ቤትን ስናስብ ኦርቶዶክሳዊት የሆነችው ቤተክርስትያን ልጆቿን ቃለ እግዚአብሔር አውቀው ባሕርየ እግዚአብሔርን ተረድተው እንዲያመልኩ፣ ሕጉን ጠብቀው ሃይማኖት፣ በምግባር እና በቱርፋት ፀንተው አምላካቸውን መስለው እንዲኖሩ የእርሱ የሆነችውን መንግስተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ በብሉይ ከአምላኳ የተቀበለችውን ሕግጋተ እግዚአብሔርን አስተምራ በሐዲስ ኪዳንም በ40 እና በ80 ቀን እያጠመቀች ለምዕመናን እንደ እድሜያቸው እና እንደ አቅማቸው ቃለ እግዚአብሔርን በስብከት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴ፣ በትርጓሜ እና በመሳሰሉት ስታስተምር፣ በእምነት ስታፀና ለክብር ስታበቃ እና ለመንግስተ እግዚአብሔር ስታዘጋጅ እዚህ ደርሳለች።

ቤተክርስትያን ዘላለማዊ የሆነውን የአምላክን ቃል ለተተኪው ትውልድ ከምታስተላልፍባቸው መንፈሳዊ ተቋማት አንዱ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ ጎልማሳዎችን በሕብረት ሆነው የሚማሩበት የቤተክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትን እና ስርዓትን አውቀው ጠብቀው የሚያቆዩበት ለቀጣይም ትውልድ የሚያስተላልፉበት ለቤተክርስትያን የሚጠቅሙ ትውልድ የሚፈራባት “በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተተኩልሽ” የሚለውን የቅዱስ ዳዊት የትንቢት ቃል የሚፈፀምበት መንፈሳዊ ተቋሟ አንዱ የሰንበት ትምህርት ቤት ነው። ያለ ጠንካራ ሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ከ2000 ዓመት በላይ ሲወረድ ሲዋረድ የመጣውን ኦርቶዶክሳዊ እምነት የሚያራምድ በሐዋርያዊት እምነት እና አስተምህሮ የፀናችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አማኝ ትውልድ ማግኘት አይቻልም። ልጆቻችንም ኦርቶዶክሳዊት እምነትን፣ ዶግማን፣ ስርአት እና ትውፊትን በሰንበት ት/ቤት ካልተማሩ ሃይማኖታችንን ጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አይቻላቸውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ልኮ ማስተማር እንደሚገባ ስርዓቱም እንደነበር በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን ይህም በዘመናችን ላለቸው ቤተክርስቲያን የሕጻናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች ማስተማሪያ ለሆነችው ሰንበት ትምህርት ቤት መነሻ የሆነ እና መሠረትነቷም መፅሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡